የግእዝ ቋንቋ የራሱ የሆነ የተወሰነ ሥርዓተ ንባብ አለው፡፡ይህ የንባብ ሥርዓቱ ከተፋለሰ ቋንቋው ለዛ ያጣል፡፡አንባቢውም ሆነ አድማጩ ምሥጢሩን ስለማይረዳው ቃሉ ትርጉም ያጣል፡፡ ስለዚህ የግእዝ መጻሕፍትን ሁሉ ለማንበብ የግእዝ ቋንቋን ሥርዓተ ንባብ መማር ይጠበቅብናል፡፡በግእዝ ቋንቋ ትምህርት ውስጥ አንዱ እና ትልቁ ክፍል የንባብ ህግጋቱነው፡፡በግእዝ ቋንቋ ሶስት ዓይነት የንባብ ዓይነቶች አሉ፡፡ ይህም አከፋፈል በንባብ ጊዜ ከድምፅ አወጣጥ አንጻር ነው፡፡
፩ ግእዝ ንባብ ፦ ይህ የንባብ ዓይነት ቃልን ከቃል እየለዩ የሚነበብበትየንባብ ዓይነት ሲሆን በአብነት ትምህርት ቤቶች የንባብ ትምህርት የመጀመሪያው የንባብ ደረጃ ነው፡፡ ፊደል የለየ ተማሪ የሚያነበው የመጀመሪያው የንባብ ዓይነት ነው፡፡ ሲነበብም ፊደልን ከፊደል እየለዩ በዝግታ ሳብ ሳብ እያለ የሚነበብ የንባብ ዓይነት ነው፡፡
፪ ውርድ ንባብ ፦ ይህ ሁለተኛው የንባብ ደረጃ ግእዝ ንባብን አንብቦ የጨረሰ ተማሪ የሚያነበው ቀጣይ ደረጃ ሲሆን የኅዘን ዜማ መልክ ያለው የንባብ ዓይነት ነው፡፡ሲነበብም ቃላትን ከቃላት እየለዩ ነው፡፡የግእዝ ንባብ ጐተት ዝግ ይል የነበረውን ሳብ ሳብ በማድረግ ይነበባል፡፡ሳቢ እና ተሳቢው ተነሽ እና ወዳቂው አንቀጹ እና አንቀጽ አጐላማሹ በየአመሉ እየተለየ የሚነበብበት የንባብ ዓይነት ነው፡፡
፫ ቁም ንባብ ፦ ከውርድ ቀጥሎ ሶስተኛው የንባብ ደረጃ ሲሆን ያለአንዳች ችግር ሕግጋተ ንባባትን ተነሽ ተጣዩን ወዳቂና ሰያፉን ጠንቅቆ በመለየት ጠበቅ ያዝ ለቀቅዘለግ ፈጠን እየተደረገ የሚነበብበት የንባብ ደረጃ ነው፡፡ ይህ የንባብ ዓይነት ዘወትር በቤተክርስቲያን በሊቃውንት ፊት ቅዱሳት መጻሕፍት የሚነበቡበት የንባብ ዓይነት ነው፡፡
በግእዝ ቋንቋ ትምህርት ውስጥ የታወቁት የንባብ ዓይነቶች አራት ናቸው፡፡ እነርሱም፦
፩, ተነሽ ፫, ወዳቂ
፪, ሰያፍ ፬, ተጣይ
አንድን ቃል የአነባበብ ሥርዓቱን ለማወቅ የሚከተሉትን መለያዎች እንጠቀማለን
መድረሻ ቀለም
የሆሄያት ተጽዕኖ
ተነባቢ ቀለም
የቃሉ ባህርይ(ስም ወይም ግስ መሆኑ) በዚህ ክፍል ለአካሄድ እንዲያመቸን ከግስ ውጭ የሆኑትን ሁሉ ስም እንላቸዋለን
፩ ተነሽ ንባብ
ተነሽ ንባብ የሚባለው እንደ ቁጣ ቃል የሚነገር ተፈላጊውን ቀለም አንስቶ አንዝሮ የሚነበብ ንባብ ነው፡፡ተነስተው የሚነበቡ ቃላትን ለመለየት የሚከተለውን ዘዴ እንጠቀማለን፡፡
ሀ, መድረሻ ቀለም ፦ ተነስተው ሊነበቡ የሚችሉ ቃላት በአምስቱ የሆሄ ስልት የጨረሱ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡እነዚህም፦
ግእዝ፣ካዕብ፣ሳልስ፣ራብዕ እና ሳብዕ ናቸው፡፡በእነዚህ ያልደረሰ ቃል ፈጽሞ ሊነሳ አይችልም፡፡
ምሳሌ፦በግእዝ ፡ ቆመ፣ገብረ፣ሐቀለ፣አንፈርዐፀ፣ሰበከ
በካዕብ፡ ቆሙ፣ገብሩ፣ሐቀሉ፣አንፈርዐፁ፣ሰበኩ
በሳልስ፡ ቁሚ፣ግበሪ፣ ሕቅሊ፣ስብኪ፣ቀድሲ
በሳብዕ፡ አሥመረቶ፣ንሴብሖ፣ይግብሮ
በግእዝ ወይም በሌሎቹ የጨረሰ ሁሉ ግን ተነስቶ ይነበባል ማለት አይደለም፡፡ለምሳሌ የሚከተሉትን ህገወጦች መመልከት እንችላለን፡፡ ህየ፣እወ፣ሠለስተ፣ክልዔተ፣አርባዕተ በግእዝ ቢጨርሱም ተነስተው አይነበቡም፡፡
አሐዱ፣ክልዔቱ፣ሠለስቱ፣አርባዕቱ በካዕብ ቢጨርሱም አይነሱም፡፡
ለ, ተነባቢ ቀለም ፦ የተነሽ ቃላት ተነባቢ ቀለማቸው ቅድመ መድረሻቸው ነው፡፡ ቅድመ መድረሻቸው ቆጣ ነዘር ብሎ ይነበባሉ፡፡ ምሳሌ፡ አእመረ፣ወረደ፣ቀተለ፣ሐወጸ
ሐ, የቃል ክፍል ፦ በአብዛኛው ተነስተው የሚነበቡ ቃላት ግሶች ናቸው፡፡
ማስታወሻ፦ ሶስት ቀለም ያላቸው በግእዝ ጀምረው ቅድመ መድረሻቸው ሳድስ በሆኑ ግሶች ሳድስ ቀለሙ ተውጦ ይነበባል፡፡
ምሳሌ፦ ገብረ፣ፈርሐ፣መርሐ፣መጽዐ
ኅረየ ዐሥርተ ወክልዔተ አርድእተ
አቅረብኩ ለከ እሳተ ወማየ ደይ እዴከ ኅበ ዘፈቀድከ
ንሴብሐከ እግዚኦ
፪ ተጣይ ንባብ
ተጣይ ቀለማት ሲነበቡ እንደ ወዳቂ ቀለም ያዝ ለቀቅ በማድረግ ነው፡፡
ሀ, መድረሻ ቀለም ፦ ተጣይ ቀላት የሚጨርሱት በሳድስ ቀለም ብቻ ነው፡፡
ምሳሌ፦ ቅዱስ፣ ኅሩይ፣ መንሱት፣ መንበር፣ ሰዋስው፣ ልብ፣ ዮም፣ ጾም
ለ, ተነባቢ ቀለም ፦ የተጣይ ቀለም ተነባቢ ቀለሙ ቅድመ መድረሻው ስለሆነ ይህን ቀለም ያዝ ቆየት በማድረግ ይነበባሉ፡፡
ሐ, የቃል ክፍል ፦ ተጣይ ቃላት በአብዛኛው ስሞች ናቸው፡፡ ከግስ የወጡ ዘሮች በአብዛኛው ተጥለው ይነበባሉ፡፡
ምሳሌ፦ ኀሩያን፣ ቡሩክ፣ ሲሳይ፣ መላእክት
ፃድቃን ወሰማዕት ጽኑዓን በሃይማኖት
ንጉሥ ወካህናት ክቡራን በኅበ እግዚአብሔር
ማስታወሻ፦ የተጣይ ቃላት ሳድስ ቀለማት ተከታትለው ሲመጡ ቅድመ መድረሻቸው ተውጦ ይነበባሉ፡፡
ምሳሌ፦ወርቅ፣ ፍቅር፣ ምድር፣ ምግብ፣ ዘርዕ፣ ቅድስት፣ ትስብእት
፫ ወዳቂ ንባብ
ይህ የንባብ ዓይነት ተፈላጊውን ቀለም ያዝ ቆየት በማድረግ ይነበባል፡፡ ወዳቂ ንባብ ወዳቂ ዜማ ባለው ድምጸ ማኀዘኒ ይነበባል፡፡
ሀ, መድረሻ ቀለም ፦ የወዳቂ ቀለማት መድረሻ ቀለማት ሰባቱም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ምሳሌ፦ በግእዝ፦ ህየ፣ አሐደ፣ ክልዔተ
በካዕብ፦ ኵሉ፣ ብሔሩ፣ ዝንቱ፣ እሙንቱ፣ እማንቱ
በሳልስ፦ ቀታሊ፣ ገባሪ፣ ዛቲ፣ ኖላዊ፣ ነጋሢ፣ ዜናዊ
በራብዕ፦ ዜና፣ መና፣ ሠረገላ፣ ተድላ፣ መክራ፣ ሀገራ
በኅምስ፦ አይቴ፣ ምናኔ፣ ሥላሴ፣ ልምላሜ፣ ትካዜ
በሳድስ፦ ዝ ብቻ ነው(በሳድስ ወዳቂ ዝ ብቻ ነው)
በሳብዕ፦ ከበሮ፣ አእምሮ፣ እፎ፣ ተዋህዶ
ለ, ተነባቢ ቀለም ፦ በወዳቂ ንባብ ጊዜ ተነባቢ ቀለሙ መድረሻ ቀለሙ ነው፡፡ተነባቢ ቀለሙን ያዝ ቆየት በማድረግ ይነበባል፡፡
ሐ, የቃል ክፍል ፦ ወድቀው የሚነበቡ በአብዛኛው ስሞች ናቸው፡፡ በዚህ ትምህርት ከግስ ውጭ ያሉትን ሁሉ በስም ስር መድበናቸዋል
፬ ሰያፍ ንባብ
ይህ የንባብ ዓይነት ተፈላጊውን ቀለም እንደ ተነሽ ንባብ አስቆጥቶ አንዝሮ ይነበባል፡፡
ሀ, መድረሻ ቀለም ፦ሰያፍ ንባብ በሳድስ ብቻ ይጨርሳል፡፡
ለ, ተነባቢ ቀለም ፦ተነባቢ ቀለሙ ቅድመ መድረሻው ነው፡፡
ሐ, የቃል ክፍል ፦ ተሰይፈው የሚነበቡ ስሞችም ግሶችም ናቸው፡፡
ምሳሌ፦ አእመረት፣ ቀተለት፣ ይወርድ፣ ይገብር፣ እቀትል፣ ቅትል፣ግበር፣ንላዕ
ኢሳያስ፣ ቶማስ፣ ገብርኤል፣ ጴጥሮስ፣ ዳንኤል፣ ቴዎፍሎስ
ገብርኤል ሰብሐ ኪያሃ
ንፁም ፆመ ወናፍቅር ቢጸነ
ማስታወሻ፦ ሰያፍ እና ተነሽ በአነባበብ አንድ ናቸው የሚለያዩት በመድረሻ ቀለማቸው ነው፡፡
ወዳቂ እና ተጣይ ሥርዓተ ንባባቸው አንድ ነው ቢባልም በተነባቢ ቀለም እና በመድረሻ ቀለም ይለያያሉ፡፡
No comments:
Post a Comment