Thursday, January 10, 2013

ምልማድ


የሚከተሉትን መራሕያን ከግሶች ጋር አዛምድ /አስተፃምር/
፩. አንትን ሀ. ነበርኩ ረ. መጽአት
፪. ውእቱ ለ. በላዕነ ሰ. ኖምክሙ
፫. አነ ሐ. ሖርኪ ሸ. ሖራ
፬. ውእቶን መ. ጸለዩ ቀ. በልዐ
፭. ይእቲ ሠ. ቀተልክን
አስተካክለህ ጻፍ / በስርዓተ- ሰዋስው/
ምሳሌ: /ኀዘነ/ ማርያም አመ /ተሰቅለ/ ክርስቶስ => ኀዘነት

 ማርያም አመ ተሰቅለ ክርስቶስ።
፩. /ኖመ/ አንተ ላዕለ አራት /አልጋ/
፪. /ሖረ/ አንትን ኀበ ደብረ ጽጌ
፫. /ቆመ/ ማርታ ወማርያም ቅድመ ቤተ መቅደስ
፬. /ኀደረ/ ፍሬ ጽድቅ ውስተ ቤተ አርድዕት /ተማሪዎች/
፭. /አርመመ/ ሚካኤል አመ ተሰቅለ አምላኩ
፮. /ተፈስሐ/ ጻድቃን በእግዚአብሔር
ወልጥ ኀበ ልሳነ ዐምሐራ /ወደ አማርኛ መልስ/
፩. ንሕነ ሖርነ ኀበ አክሱም ወላስታ
፪. አንቲ ውእቱ እመ ብርሃን
፫. ማርያም ወለደት ወልዳ ዘበኩራ
፬. አንተ ወአነ ሰማዕነ ቃለ እግዚአብሔር
፭. እለመኑ /እነማን/ ውእቶሙ ዘሖሩ ኀበ ገዳመ ሲና
ወደ ግእዝ መልስ /ወልጥ ኀበ ልሳነ ግእዝ/
፩. ወደ ጸሎት ቤት ሄድን።
፪. እኔ ነኝ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሄድኩ። /ዘ = የ/
፫. እነርሱ በኅብረት ተቀመጡ። /ኅቡረ = በኅብረት/
፬. ቶማስ እና ጴጥሮስ መምህራን ናቸው።
፭. ማርያም ድንግል የአሮን በትር /በትር = በትር/ ናት።
፮. አንተ የክርስቶስን ወንጌል ሰበክህ።
፯. አንተ ሰባኪ አይደለኽም።
፪.፩.፫. መራሕያን እንደ አመልካች ቅጽል
የመራሕያን ሌላው አገልግሎታቸው አንድን ነገር ወይም አካል በተባዕትና በአንስት፣ በማይታይና በሚታይ፣ በቅርብ ሩቅና በቅርብ ቅርብ አመልካች ጠቋሚ እየኾኑ መነገራቸው ነው። በሊቃዉንት መጻሕፍት ጉልት እየተባሉ ይጠቀሳሉ።
መደባቸዉም ሦስት ሲሆኑ እነዚኽም፦
፩. ተናጋሪን /እኔን ባይ/ አመልካቾች
፪. የማይታይ አመልካቾች
፫. የሚታይ አመልካቾች ናቸው። በተጨማሪ የቅርብ ሩቅ አመልካች ሆነው ሲገለጹ ደግሞ፦
ውእቱ ዝኩ ተብሎ ይገለጻል። ትርጉሙም ያ
ይእቲ እንትኩ >> >> ያቺ
ውእቶሙ እልኩ >> >> እኒያ /እነዚያ/
ውእቶን እልኮን >> >> እኒያ /ለሴቶች/
የሚከተሉትን ቃላት በማጥናት ከላይ ባየናቸው የመራሕያን አገልግሎት የራሳችሁን መልመጃዎች ሥሩ።
ሀ. ቃላት
ከመ = እንደ ወ = እና ጥቀ = እጅግ
አይቴ = ወዴት ማዕዜ = መቼ ናሁ = አሁን ፣ እነሆ
ምስለ = ጋር ምንት = ምን
እም = ከ በእንተ = ስለ
አላ = እንጂ ዝየ = እዚህ
ህየ = እዚያ ዮም = ዛሬ
ጌሠም = ነገ ትማልም = ትላንት
ዘ = እንተ = የ እለ ፣ ዘ = የ /ለብዙ/
(ዘሖረ = እንተ ሖረ =የሄደ) ምሳሌ: እለ ሖሩ = ዘሖሩ = የሄዱ
የቤተሰብእ ስም
ነጠላ ብዙ
አብ = አባት አበው = አባቶች
እም = እናት እማት = እናቶች
ወልድ = ልጅ /ወንድ/ ውሉድ = ልጆች
ወለት = ሴት ልጅ አዋልድ = ሴት ልጆች
እኅት = እኅት አኀት = እኅቶች
እኁ = ወንድም አኀው = ወንድሞች
አመት = ሴት አገልጋይ አእማት = ሴት አገልጋዮች
ገብር = ወንድ አገልጋይ አግብርት = ወንድ አገልጋዮች
ለ. የግስ ቃላት
ሖረ = ሄደ ፤ ቆመ = ቆመ ፤ ኖመ ፣ ደቀሰ = ተኛ
ጸለየ = ልመና አቀረበ ፤ ሰአለ = ለመነ ፣ ጠየቀ ፤ ነበረ = ተቀመጠ ፤ ኀደረ = አደረ
አርመመ = ዝም አለ ፤ ተፈስሐ = ተደሰተ ፤ ሰብሐ = አመሰገነ
በልዐ = በላ ፤ መጽአ = መጣ ፤ ቀተለ = ገደለ ሰትየ = ጠጣ
ምልማድ /መልመጃ/
የ “ሀ” ን ቃላት ከ “ለ” ቃላት ጋር /መራሕያኑን ከግሶች/ አዛምድ /አስተፃምር ቃላተ “ሀ” ምስለ ቃላተ “ለ”/
“ሀ” “ለ”
፩. አንትን አ. ነበርኩ
፪. ውእቱ በ. በላዕነ
፫. አነ ገ. ሖርኪ
፬. ውእቶን ደ. ቀተልክን
፭. ይእቲ ሀ. መጽአት
፮. ንሕነ ወ. ኖምክሙ
፯. አንቲ ዘ. ሖራ
፰. ውእቶሙ ሐ. በልዐ
፱. አንትሙ ጠ. ጸለዩ
ወልጥ ኀበ ልሳነ ዐምሐራ /ወደ አማርኛ ለውጥ/
፩. ንሕነ አብደርነ /አብደረ = መረጠ/ ንትገደፍ /ገደፈ = ተወ ፣ ጣለ/ ውስተ ቤተ እግዚአብሔር እም ንንበር ውስተ ቤተ ኃጥአን።
፪. አንቲ ውእቱ መሶበ ወርቅ ንጹሕ
፫. አንተ ወአነ ሖርነ ኀበ መካነ ምስያጥ /ገበያ/
፬. ወለተ ማርያም ነጸረት መንገለ /ወደ/ ምስራቅ
፭. አንትሙ ሖርክሙ ኀበ ኢየሩሳሌም
፮. እለመኑ ውእቶሙ ዘነገዱ ኀበ ብሔረ እስራኤል
፯. ንሕነ ጸለይነ በእንተ ዴር ሡልጣን
፰. ውእቶሙ ተዐቀቡ እም ኤድስ
፱. አንትሙ ሰብሕዎ ለእግዚአብሔር
፲. አነ ደቀስኩ ላዕለ አራትየ
ወልጥ ኀበ ልሳነ ግእዝ
፩. አንተ አውሮጳዊ አይደለህም።
፪. የእናትህ ስሟ ማነው?
፫. ወንድሞች ወደ ቤተ ክርስቲያን መጡ።
፬. ሰሎሞን ወደ አባቶች ሄደ።
፭. ዝም ብሎ ተቀመጠ።
ትውውቅ /ሰላምታ/
ዜና ሥላሴ ቤዛ ማርያም
ሰላም ለከ እኁየ ወሰላም ለከ እኁየ
ሰላም ላንተ ይሁን ወንድሜ ሰላም ላንተም ይሁን
እፎ ሐሎከ እግዚአብሔር ይሰባሕ
እንዴት አለህ? እግዚአብሔር ይመስገን
መኑ ስምከ ቤዛ ማርያም ውእቱ ስምየ
ስምህ ማነው? ስሜ ቤዛ ማርያም ነው
ወመኑ ስመ አቡከ ዘድንግል ውእቱ ስመ አቡየ
የአባትህስ ስም ማነው? የአባቴ ስም ዘድንግል ነው
ወመኑ ስመ እምከ አስካለ ማርያም ውእቱ ስመ እምየ
እም አይቴ መጻእከ እም ጎጃም
ከየት ነው የመጣህ? ከጎጃም
እስፍንቱ አዝማኒከ ዕሥራ ወአሐዱ
ዕድሜህ ስንት ነው? ሃያ አንድ
ናሁ…ኀበ አይቴ ውእቱ ዘተሐውር ኀበ ከኒሳ
አሁን ወደ የት ነው የምትሄደው? ወደ ቤተ ክርስቲያን
እም አይቴ ውእቱ ዘትመጽእ ናሁ
እም መካነ ምሥያጥ አኹን ከየት ነው የምትመጣው?
ከገበያ ኦሆ = እሽ
ሰናይ ምስየት ለኲልነ
መልካም ምሽት ለኹላችን

ግእዝ ክፍል ሁለት : ሰዋስወ ግእዝ


ሰዋስወ ግእዝ

፪.፩. መራሕያን
መርሐ /መራ/ ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን መሪዎች ፊታውራሪዎች የሚለውን ትርጉም ይይዛል። መራሕያን የሚባሉት በግእዝ ልሣን አስር ናቸው።
እነሱም ፦
አነ ………………………………እኔ
አንተ ……………………………አንተ
አንቲ ……………………………አንቺ
ውእቱ ……………………………እሱ
ይእቲ …………………………….እሷ
ንሕነ ……………………………..እኛ
አንትሙ ………………………….እናንተ /ለቅርብ ወንዶች/
አንትን ……………………………እናነተ /ለቅርብ ሴቶች/
ውእቶሙ /እሙንቱ/ …………….እነርሱ /ለሩቅ ወንዶች/
ውእቶን /እማንቱ/ …………………እነርሱ /ለሩቅ ሴቶች/
የመራሕያን አገልግሎት ሦስት ዓይነት ነው፡፡ ይኸዉም ፦
፩.፩. ተውላጠ ስም በመሆን
፩.፪. የመሆን ግስ /ነባር አንቀጽ/ በመሆንና
፩.፫. አመልካች ቅጽል በመሆን
፪.፩.፩. መራሕያን ምድብ ተውላጠ - ስሞች / pronouns /

መደብ ጾታ ነጠላ ቁጥር ብዙ ቁጥር
ሣልሳይ /ሦስተኛ መደብ/ ተባዕታይ ውእቱ ውእቶሙ /እሙንቱ/
አንስታይ ይእቲ ውእቶን /እማንቱ/
ካልኣይ /ኹለተኛ መደብ/ ተባዕታይ አንተ አንትሙ
አንስታይ አንቲ አንትን
ቀዳማይ /፩ኛ መደብ/ የወል አነ ንሕነ

በስም ፋንታ ተተክቶ የሚያገለግል ቃል ተውላጠ-ስም ይባላል። መራሕያን እንደ ተውላጠ-ስም ሲሆኑ በስም ፋንታ ተተክተው የሚነገሩ የርባታ መደቦች ናቸው። እነሱም የአካል፣ የስምና የስም አጸፋ እየሆኑ በወንድና በሴት፣ በሩቅና በቅርብ፣ በነጠላና በብዙ የሚነገረውን ርባታ ያሳያሉ። አስሩም መራሕያን በነጠላና በብዙ፣ በወንድና በሴት፣ በሩቅና በቅርብ ሲከፈሉ ሦስት መደብ ይሆናሉ።
ይኸዉም፦
፩. ቀዳማይ መደብ / 1st person/ አንደኛ መደብ፡ የወል ጾታ
አነ => እኔ = I
ንሕነ => እኛ = we
፪. ካልኣይ መደብ /2nd person/ ኹለተኛ መደብ፡
አንተ => በቁሙ = you
አንቲ => አንተ = you
አንትሙ => እናንተ = you (ለቅርብ ወንዶች)
አንትን => እናንተ = you (ለቅርብ ሴቶች)
፫. ሣልሳይ መደብ / 3rd person / ሦስተኛ መደብ፡
ውእቱ => እሱ = He
ይእቲ => እሷ = She
ውእቶሙ => እነሱ (እነዚያ) = They (ለሩቅ ወንዶች)
ውእቶን => እነሱ (እነዚያ) = They (ለሩቅ ሴቶች)
፩.፩. መራሕያን ምድብ ተውላጠ-ስሞች በዐረፍተ- ነገር
ተውላጠ-ስሞች ቀደሰ፣ ሖረ እና ሰገደ በሚሉት ቀዳማይ አንቀጾች ዐረፍተ- ነገር ሲመሠርቱ፦
ሀ. ቀደሰ / ቀዳማይ አንቀጽ፡ past tense/
አነ ቀደስኩ - እኔ አመሰገንሁ
አንተ ቀደስከ - አንተ አመሰገንህ
አንቲ ቀደስኪ - አንቺ አመሰገንሽ
ውእቱ ቀደሰ - እሱ አመሰገነ
ይእቲ ቀደሰት - እሷ አመሰገነች
ንሕነ ቀደስነ - እኛ አመሰገን
አንትሙ ቀደስክሙ - እናንተ አመሰገናችሁ
አንትን ቀደስክን - እናንተ አመሰገናችሁ (ለሴቶች)
ውእቶሙ ቀደሱ - እነሱ አመሰገኑ
ውእቶን ቀደሳ - እነሱ አመሰገኑ (ለሴቶች)
ማስታወሻ
• ውእቱ / ቀደሰ/ እና ይእቲ /ቀደሰት/ ከሚሉት ውጭ በሌሎች መራሕያን "ሰ" የሚለው ፊደል ወደ ሳድስ፣ ራብዕና ሳብዕ ይለወጣል፡፡
ለ. ሖረ = ሄደ /went/ ፣ ኀበ = ወደ
አነ ሖርኩ ኀበ ቤተ እግዚአብሔር - እኔ ወደ እግዚአብሔር ቤት ኼድኩ።
አንተ ሖርከ ኀበ ቤተ እግዚአብሔር - አንተ ወደ እግዚአብሔር ቤት ኼድክ።
አንቲ ሖርኪ ኀበ ቤተ እግዚአብሔር - You went to church (house of God).
ውእቱ ሖረ ኀበ ቤተ እግዚአብሔር - He went to church.
ይእቲ ሖረት ኀበ ቤተ እግዚአብሔር
ንሕነ ሖርነ ኀበ ቤተ እግዚአብሔር
አንትሙ ሖርክሙ ኀበ ቤተ እግዚአብሔር
አንትን ሖርክን ኀበ ቤተ እግዚአብሔር
ውእቶሙ ሖሩ ኀበ ቤተ እግዚአብሔር
ውእቶን ሖራ ኀበ ቤተ እግዚአብሔር
ሐ. ሰገደ = ሰገደ ፣ቅድመ = ፊት ለፊት
አነ ሰገድኩ ቅድመ ቤተ መቅደስ - በቤተ መቅደስ ፊት ሰገድሁ ።
አንተ ሰገድከ ቅድመ ቤተ መቅደስ - You fell on in front of church.
አንቲ ሰገድኪ ቅድመ ቤተ መቅደስ
ውእቱ ሰገደ ቅድመ ቤተ መቅደስ
ይእቲ ሰገደት ቅድመ ቤተ መቅደስ
ንሕነ ሰገድነ ቅድመ ቤተ መቅደስ
አንትሙ ሰገድክሙ ቅድመ ቤተ መቅደስ
አንትን ሰገድክን ቅድመ ቤተ መቅደስ
ውእቶሙ ሰገዱ ቅድመ ቤተ መቅደስ
ውእቶን ሰገዳ ቅድመ ቤተ መቅደስ
ማስታወሻ
የግሱ መጨረሻ ፊደል ‹ከ› ፣‹ቀ› ፣‹ገ› ን የመሰለ ከሆነ ከዚያው ላይ ፊደሉን በማጥበቅ (አነ ፣አንተ ፣አንቲ፣ አንትሙ፣ አንትን ሲሆኑ) ይነበባል። ምሳሌ ሰበከ ብሎ አነ ሰበኩ ይባላል (ኩ ጠብቃ ትነበባለች) እንጅ አነ ሰበክኩ አይባልም። አነ አጥመቁ ይላል እንጅ አነ አጥመቅኩ አይልም። ስለሆነም ማጥበቅ አለብን።
፪.፩.፪. መራሕያን እንደ ነባር አንቀጽ / verb to be/
ነባር አንቀጽ ሲባል ማሰሪያ ግስ ማለት ነው። መራሕያን በአንቀጽነታቸው እየተተረጎሙ ሲፈቱ ማሠሪያ ይሆናሉ። ይኸዉም፦
ውእቱ = ነው፣ ኾነ፣ ነበረ፣ ኖረ፣ ይኑር፣ ነሽ፣ ነኝ፣ ነኽ፣ ናችሁ፣ ነበራችሁ
ይእቲ = ናት፣ ነበረች
ውእቶሙ(እሙንቱ) = ናቸው፣ ሆኑ፣ ነበሩ፣ ኖሩ፣ ይኑሩ ( ለወንዶች)
ውእቶን(እማንቱ) = ናቸው፣ ነበሩ (ለሴቶች)
አንተ = ነህ፣ ሆንክ፣ ነበርክ፣ ኖርክ፣ ኑር
አንቲ = ነሽ፣ ኾንሽ፣ ነበርሽ፣ ኖርሽ፣ ኑሪ
አንትሙ(ተባዕት) = ናችኹ፣ ኾናችኹ፣ ነበራችኹ፣ ኖራችኹ፣ ኑሩ
አንትን(አንስት) = ናችኹ፣ ኾናችኹ፣ ነበራችኹ፣ ኖራችኹ፣ ኑሩ
ንሕነ = ነን፣ ኾንን፣ ነበርን፣ ኖርን፣ እንኑር
አነ = ነኝ፣ ኾንኩ፣ ነበርኩ፣ ኖርኩ፣ ልኑር
ምሳሌ፦
አነ ውእቱ ጒንደ ወይን = እኔ የወይን ግንድ ነኝ።
አነ ውእቱ ኖላዊ ኄር = እኔ ቸር ጠባቂ ነኝ።
አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም= የአዳም /ለአዳም/ ተስፋው አንቺ ነሽ።
አንተ ውእቱ ዕጣን ኦ መድኃኒነ = መድኃኒታችን ሆይ አንተ ዕጣን ነህ።
ማርያም ይእቲ መሠረተ ሕይወት = ማርያም የሕይወታችን መሠረት ናት።
ናሆም ወሚልክያስ ነቢያት ውእቶሙ /እሙንቱ/ = ናሆምና ሚልክያስ ነቢያት ናቸው።
አስቴር ወሶስና ቅዱሳን ውእቶን /እማንቱ/ = አስቴርና ሶስና ቅዱሳን ናቸው።
ውእቱ ለዋጭ ተለዋጭ ባሕርይ ስላለው በተባዕትና በአንስት በብዙና በነጠላ አፈታት ይፈታል። እንዲህ ማለት በነባር አንቀጽነቱ የሚከተሉትን ትርጉም ሊያስገኝ ይችላል። በዐረፍተ- ነገር እየገባ ሲታይ የትኛውን ትርጉም እንደያዘ ዐመሉን ማስተዋል ያስፈልጋል።
ውእቱ = ነው፣ ናት፣ ናቸው /ተ/አ/፤
= ነኽ፣ ነሽ፣ ናችኹ /ተ/አ/ ፤
= ነኝ፣ ነን፣ ይኾናል
ሥርዓተ ዐረፍተ- ነገር በምሳሌ፦
• ቅድስት ይእቲ ኤልሳቤጥ = ኤልሳቤጥ ቅድስት ናት
• ኤልሳቤጥ ቅድስት ይእቲ
• ነቢይ ውእቱ ሕዝቅኤል
• ሕዝቅኤል ነቢይ ውእቱ
ውእቱ ለሚለው አሉታው አኮ /አይደለም/ ነው
ለምሳሌ፦ አኮ ነቢይ ሕዝቅኤል
ተጨማሪ ምሳሌዎች:
አነ ውእቱ ፍኖተ ጽድቅ = እኔ የእውነት መንገድ ነኝ
አንተ ውእቱ ቤዛ ኵሉ ዓለም = አንተ የዓለም ሁሉ ቤዛ ነህ
ጳዉሎስ ወጴጥሮስ መምህራን ውእቶሙ
ሰሎሜ ወኤልሳቤጥ ቅዱሳት ውእቶን

አበዊነ መሀሩነ ልሳነክሙ ወቃለ እግዚአብሔር

ግእዝ ክፍል አንድ : የግእዝ ፊደላትና ትርጉማቸው

የግእዝ ፊደላትና ትርጉማቸው

ፊደል ስመ ትርጓሜሁ የስማቸው ትርጓሜ 
‹‹ሀ››...ብሂል…..........ሀልዎቱ ለአብ…........የአብ አኗኗሩ
‹‹ለ››. .ለብሰ ሥጋነ ወፆረ ሕማመነ...የእኛን ሥጋ ለብሶ ሕማማችንን ተሸከመ
 ‹‹ሐ››.........ሕያው እግዚአብሔር…..እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ነው 
‹‹መ››…...............መጽአ ውስተ ዓለም...........ወደ ዓለም መጣ
‹‹ሠ››.......ሠረቀ እም ድንግል በሥጋ.........ከድንግል በሥጋ ተወለደ 
‹‹ረ››............ረግዐ ሰማይ ወምድር..............…ሰማይና ምድር ፀና
‹‹ሰ››…..........ሰፋኒ እግዚአብሔር......እግዚአብሔር ምሉዕ ነው 
‹‹ቀ››…...............ቀዳሚሁ ቃል…................መጀመሪያ ቃል ነበር
‹‹በ››…......ባዕል እግዚአብሔር........…እግዚአብሔር ባዕለ ፀጋ ነው 
‹‹ተ››…................ተሰብአ ወተሠገወ...........................…ፍጹም ሰው ሆነ
‹‹ኀ››...................ኃያል እግዚአብሔር….....................እግዚአብሔር ኃያል ነው
 ‹‹ነ››...ነሥአ ሥጋ እም ቅድስት ድንግል...ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ነሳ 
‹‹አ››...................አብ አሐዜ ኵሉ..........................…ዓለምን የያዘ አብ ነው
‹‹ከ››..................ከሃሊ እግዚአብሔር........................…እግዚአብሔር ቻይ ነው 
‹‹ወ››....ወረደ ወተሠገወ.…ከሰማየ ሰማያት ወረደ ሰውም ሆነ
‹‹ዐ››..................ዐቢይ እግዚአብሔር.....................…እግዚአብሔር ታላቅ ነው
‹‹ዘ››..................ዘምሩ ለእግዚአብሔር.................…እግዚአብሔርን አመስግኑ 
‹‹የ››…..የማነ እግዚአብሔር........የእግዚአዘብሔር እጅ ድንቅ ነገር አደረገች 
‹‹ደ››........ደመረ ሥጋነ ምስለ መለኮቱ...…ሥጋችንን ከመለኮቱ ጋር አዋሐደ 
‹‹ገ››….............ገብረ ሰማየ ወምድረ....................….ሰማይንና ምድርን ፈጠረ 
‹‹ጠ››…ጣዕሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር...እግዚአብሔር ቸር መሆኑን አውቃችሁ ቅመሱ
‹‹ጰ››…........ጰራቅሊጦስ…..............መንፈስ ቅዱስ
‹‹ጸ››…...........ፀሐየ ጽድቅ እግዚአብሔር…..... እግዚአብሔር እውነትኛ ፀሐይ ነው
 ‹‹ፈ››…..........ፈጠረ ሰማየ ወምድረ…....................ሰማይንናምድርን ፈጠረ
‹‹ፐ››…........ፓፓኤል እግዚአብሔር…...................ፋኖስ መንፈስ

Friday, January 4, 2013

የልደት በዓል

ቃልም ሥጋ ሆነ” [ዮሐ1:1]
በአንድ ወቅት ነቢዩ ሚክያስ ሕዝቡን ሲያስተምር ውሎ ወደ ማታ በቤተልሔም በኩል ሲያልፍ ከተማዋ እጅግ ጎስቁላ አየና እያዘነ እንዲህ አለ። “አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ ከይሁዳ ነገሥታት ትንሿ ብትሆኚም ንጉሥ በአንቺ ይወለዳልና ታላቅ ነሽ!” ሚክያስ [5: 2]
እነሆ ነቢዩ ሚክያስ ትንቢቱ ከመፈጸሙ ከ700 ዓመታት በፊት ጌታችን በቤተልሔም እንደሚወለድ ተንብዮ ነበር። ነቢዩ እንዳለውም ቤተልሔም ታላቅ ከተማ ሆናለች።
/ጌታ ተወለደባት፣ ታላቁ ዘሩባቤል ነገሠባት/
* ቤተልሔም ኤፍራታ ቤተሕብስት ስትባል የእንጀራ ቤት ማለት ነው። በእንጀራ ቤት /በቤተልሔም/ የተወለደው ጌታችን “እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ” እያለ ሕይወትን ሰጥቶናልና። አንድም ቤተልሔም የእመቤታችን ምሳሌ ነው፤ እንዴት? ቢሉ ቤተልሔም የእንጀራ ቤት ስለሆነ እመቤታችንም ለአማናዊው እንጀራ ለጌታችን ማደሪያው ስለሆነች ነው።
እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሰን!
የጌታችንን ልደት ከብሥራት አንሥቶ በሰፊው የተረከልን ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ነው፡- “በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች” በማለት የልደቱን ዘገባ ይጀምራል፡፡ በወቅቱ ዓለምን ሁሉ የምትገዛው ሮም ነበረች፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ቄሣር በሚል መዐርግ ይጠራ ነበር፡፡ መንበሩም ያለው በሮም ሲሆን ዓለሙንም የሚያስተዳድረው በአጥቢያ ነገሥታት በኩል ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ዓለሙን የሚገዛው ከመንበሩ ሳይንቀሳቀስ ነው፡፡ በመልእክተኞቹ አማካይነት ዓለሙን ይገዛል፡፡ ጌታችን የተወለደው ከዘመን መርጦ በሮም አገዛዝ ዘመን ነው፡፡ የሮም አገዛዝ ለእግዚአብሔር መንግሥት ገላጭነት አለው፡፡ ይኸውም፡- እግዚአብሔር አብ ከሥፍራው ሳይናወጥ ይኖራል፤ ቃሉን ወይም ልጁን እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን እየላከ ዓለምን ይገዛል፡፡ ወደዚህ ዓለም በሥጋ የመጣው እግዚአብሔር ወልድ ነው፡፡ እርሱ ካረገ በኋላም መንፈስ ቅዱስ መጥቷል። ክርስቶስ በትምህርቱ፣ በቤዛነቱ ዓለሙን ገዛ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በጸጋው በተአምራቱ እንዲሁም በክርስቶስ ቃሎች ዓለምን ይገዛል፡፡ እንዲህ ሲሆን ግን የሥላሴ መንግሥት አንዲትና እኩል ናት፡፡
ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች [ኢሳ. 7: 14]
በጥሊሞስ ፈላደልፈስ 72 ሊቃውንትን በአሌክሳንድርያ አካባቢ በምትገኘው በፋሮስ ደሴት ላይ በ72 ቀናት ውስጥ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ከዕብራዊያን ወደ ጽርእ /ግሪክ/ እንዲተረጎም አደረገ። ከ72ቱ ሊቃውን ሁለቱ መንገድ ላይ ሲሞቱ ሌሎቹ ሊቃውንት ብሉይ ኪዳንን ለመተርጉም እየገሰገሱ ንጉሥ በጥሊሞስ ጋር ደረሱ!
ከነዚህ 70 ሊቃውንት አንዱ አረጋዊ ስምኦን ነው። እነሆ ሰባው ሊቃውንት በሙሉ የየራሳቸውን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በእጆቻቸው ይዘዋል፤ አሁን ሊተረጉሙ ብዕራቸውን ሁሉም ያዙ!
ለአረጋዊ ስምኦን የደረሰው የብሉይ ኪዳን ወንጌል እየተባለ የሚታወቀው “ትንቢተ ኢሳይያስ” ነበር። ሊቁ አረጋዊ ስምኦንም እነሆ ትንቢተ ኢሳያስን ሊተረጉም ፩ዱ ብሎ ጀመረ። እስከ ፯ኛው ምዕራፍ በደህና ደረሰ፤ ምዕራፍ ፯ ላይ ሲደርስ ግን ሊቁ ግራ ተጋባ! እንዴት ሊሆን ይችላል እያለ ተገረመ! ምን ይሆን ያነበበው?
“ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ወይሰመይ ስሙ አማኑኤል” ይህችን ቃል አነበበና አሁንም ሊቁ ተደመመ!!! እንዲህ ማለት ነበርና፦
ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች [ኢሳ. 7: 14]
ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች! ከዚህ በፊት ሆኖ አያውቅም፤ በግዜውም አልተደረገም ወደፊትም አይደገምም አለና ሊቁ አሁንም ተደመመ! አሁን ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች ብዬ ብተረጉመው አይደለም በጥሊሞስ የአሕዛብ ንጉሥ ቀርቶ የእስራኤል ንጉሥ ቢሆንስ ያምነኛልን? ብሎ ሊቁ አሰበ። እናም ድንግል ትፀንሳለች የሚለውን ሰርዞ ሴት ልጅ ትፀንሳለች ብሎ ፃፈው። ሊቁ ስምኦን እስከ ፯ኛው ምዕራፍ ስለፃፈ ደከመው መሰል ሸለብ አደረገው።
ትንሽ እንዳረፈም ነቃ፤ ካቆመበት ሊቀጥል ቢል እነሆ የሰረዘው ተመልሶ “ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች” የሚለውን አነበበ። በጣም ደክሞኛል ማለት ነው? የሰረዝኩት መስሎኝ ነበር አለና አሁንም ደግሞ ሰረዘውና አሸለበ። እንዲህ እያለ “ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች” የሚለውን ፫ ግዜ ቢሰርዘው ፫ ግዜ “ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች”የሚል ተጽፎ አነበበ።
በመጨረሻም ሊቁ አረጋዊ ስምኦን የተጠራጠረውን ይህን “ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች” የሚለውን ቃል በዓይኑ ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ ገለፀለት። ስለዚህም ሉቃስ በወንጌሉ እንዲህ አለ፦ የጌታን መወለድ በዓይኑ ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ ያደረበትና የገለጠለት ሰው ነበር [ሉቃስ 2: 26]
አረጋዊው ስምኦን እጅግ የተደነቀበትን ቃል ለ500 ዓመታት ያህል በተስፋ ጠበቀ፤ እነሆ በዓይኑ የሚያይበት ግዜም ደረሰ፤ ይህም ጌታችን ከአንዲት የ15 አመት ታናሽ ገሊላዊት ብላቴና በህቱም ድንግልና በቤተልሔም በኤፍራታ መወለዱ ነው!!!
ነቢዩ ኢሳያስ ስለ ፅዮን /ስለእመቤታችን/ ዝም አልልም እያለ በቤተልሔም ኤፍራታ ተገኘና የመላዕክቱን የእረኞቹን ዝማሬ ሰማና “ናሁ ድንግል ትፀንስ” እነሆ ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች አለና የጌታን ልደት በዓይኑ ሊያይ ናፈቀና ትንቢቱ ከመፈፀሙ ከ700 ዓመታት በፊት አስቀድሞ ተነበየ፤ የዘመኑ ሰዎች አልታደሉምና እንዴት ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች አሉና መጋዝ አመጡና ኢሳያስን ያዙና እነሆ ሥጋውን ለሁለት በመጋዝ ቆራረጡት!
ነቢዩ ኢሳያስ የተነበየውን ትንቢት በዓይኑ አላየም። የኢሳያስን ትንቢት የተረጉመው አረጋዊ ስምኦን ግን በዓይኑ አየ፤ አንዳንድ ጊዜ እኛ ከምንናገረው ይልቅ ሰምተው የሚተረጉሙት የእግዚአብሔርን ቸርነት በዓይናቸው ያያሉ!
አረጋዊ ስምኦን “ድንግል በድንግልና ትፀንሳለች” የሚለውን ትንቢት ተረጎመ በዓይኑም አየ አመነም! እንዲህም አለ ፦
“ዓይኖቼ ማዳኑን አይተዋልና ይገባዋል ክብርና ምስጋና” ሉቃስ [2: 30]
የክርስቶስን ልደት ስናነሣ ፈረንጆቹ ስለ ገና አባትና ስለ ገና ዛፍ ስለ በረዶ ያስባሉ። በአገራችንም ስለ ገና ጨዋታ ይታሰባል፡፡ በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናትም ገና የሕፃናት ነው ተብሎ ለሕፃናት ከረሜላ በማደል ይጠናቀቃል፡፡ የክርስቶስ ልደት ግን የመላው የሰው ዘር እንደገና የተወለደበት እንጂ ተራ የሕፃን በዓል አይደለም፡፡ የልደትን በዓል ማክበር ብቻውን ክርስቲያን አያሰኝም፡፡ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሆኑት የፍልስጤም አስተዳዳሪዎች የቀድሞ ያሲን አራፋት አሁን ደግሞ ማሕሙድ አባስ በቤተ ልሔም ተገኝተው ያከብሩታል፡፡ የእኛ አከባበር ከዚህ የላቀ ካልሆነ ድካም ብቻ ነው፡፡ የተወለደውን ሕጻን በቁሳቁስ ሳይሆን በሕይወታችን ልናከብረው፤ ደስታችንም በመብልና በመጠጥ ሳይሆን በፍቅሩ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ብዙዎች እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሰን እያሉ ይዘፍናሉ፣ ይጨፍራሉ፣ ይሰክራሉ፡፡ ክርስቶስ ግን የተወለደው ዘፈን፣ ኃጢአትና ዝሙት ከተባሉት የጨለማ ሥራዎች ሊያድነን መሆኑን ገና አላወቁም፡፡ ይልቁንም ቃሉ፡- “የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ÷ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና” ይላል (ዘፀ. 20÷7)፡፡ የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ መጥራት ማለት በስሙ በተሰየሙ ቀናት ኃጢአትን መሥራት ነው፡፡ ይህ እግዚአብሔርን የኃጢአታችን ተባባሪ ማድረግ ነው፡፡ ፍርዱም ከፍ ያለ ነው።ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ምህረቱ ሊነገር አይታሰብም ከቶም አይጀመርም። የዘመናት ጌታ ዘመኑ በተፈጸመ ጊዜ ከድንግል ተወልዶ “ዓመተ ምህረት” ሰጥቶናልና። እንደ ዓባይ እንደ ጣና ባለ ባሕር ጽውዕ ምሉ ማር ጽውዕ ምሉ ቅቤ ቢጨምሩ ከመልኩ ከጣዕሙ እንደማይለውጠው ኹሉ የእኛም ኃጢአት የእግዚአብሔርን ቸርነት አይለውጠውም። አንድም ወኃበ በዝንቱ ኃጢአት ህየ ፈድፈደት ጸጋሁ ለእግዚአብሔር እንዲል ኃጢአት ከበዛች ዘንድ የእግዚአብሔር ጸጋ በዛች። ሮሜ [1: 23] እንዴት ቢሉ በኃጢአቱ ቦታ ጽድቁ ስለገባ። አንድም ጌታ ሰው መኾኑ በምልአተ ኃጢአት ነው እንጂ በጥንተ አብሶ አይደለምና።/ከአዳምና ከሔዋን ዠምሮ በዘር የሚተላለፍ ኃጢአት ጥንተ አብሶ ይባላል/ በጥንተ አብሶ ሰው ኾኖ ቢኾን አዳምንና ሔዋንን ብቻ ለማዳን ሰው ኾነ እንጂ እኛስ በመስዋዕታችን በግዝረታችን በጸሎታችን ዳንን ባልን ነበር። ግዝረቱ መስዋዕቱ እንዳላዳነ ካሳየን በኋላ ከድንግል ተወልዶ ሰው ኾነ።
ኃጢአት ከበዛች ዘንድ የእግዚአብሔር ጸጋ በዛች! እንዲኽ ከኾነ የእግዚአብሔር ጸጋ ይበዛልን ዘንድ ኃጢአት እንስራ እንላለንን?
ሐሰ።
አንልም።
ቸርነቱን አድንቀን በንስሐ እንመለሳለን እንጂ።
የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱ የዓለምን ታሪክ ለሁለት የከፈለ ነው፡፡ ዛሬ በክርስቶስ የሚያምነውም ሆነ የማያምነው ዓለም ዘመንን ሲቆጥር ከክርስቶስ ልደት በፊት ከክርስቶስ ልደት በኋላ እያለ ይቆጥራል፡፡ ለምን? ስንል ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ዘመን ለሁለት ስለከፈለው ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው ዘመን ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኵነኔ ሲባል ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለው ዘመን ግን ዓመተ ምሕረት ተብሏል፡፡
ዲያቢሎስ በሥጋ ከይሲ ተሠውሮ ቢያስት ጌታችንም በሥጋ ብእሲ ሥግው ኾኖ አዳነን! አምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም ከእመቤታችን ያላባት መወለዱ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለናት መወለዱን ያስረዳል። ልደት ቀዳማዊ ተዓውቀ በደኃራዊ ልደት እንዲል። ሰብአ ሰገል በኮከብ እየተመሩ ወደ ቤተልሔም መጡ። ኮከብ የተባለው የማታ ኮከብ ሳይኾን መልአክ ነው። እንዴት ታወቀ ቢሉ እነኾ ኮከብ በማታ እንጂ በቀን አይታይም። ሰብአ ሰገልን ግን በቀን መራቸው። ኮከብ ወደ ምዕራብ ይሄዳል እንጂ ወደ ምስራቅ አይመራም። ሰብአ ሰገልን ግን ወደ ምስራቅ መራቸው። ኮከብ ርቀት አለው ሰብአ ሰገልን ግን ከአናታቸው ጥቂት ከፍ ብሎ መራቸው። ይህስ ኾኖ ለምን መልአኩ በኮከብ ተመሰላቸው ቢሉ ሰብአ ሰገል የኮከብ አጥኚ ወይንም አስትሮኖመርስ ስለነበሩ በለመዱት ነገር ለመሳብ ነው።
“አውራ ጣቱን አሰረችው”
እመቤታችን ጌታን በወለደችው ጊዜ የጌታን አውራ ጣት አስራ ነበር። ምሥጢሩ ምን ይሆን ቢሉ እነሆ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ እንዲህ አድርገው ይገንዙሃል ስትል ነው። አንድም መንፈስ እንዳይደለ ለማሳየት ነው። መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና አይታሰርም ነበር። አንድም በጨርቅ ጠቀለለችው። ይህም ምሥጢሩ አንድ ነው። (የዮሴፍና ኒቆዲሞስ መግነዝ ፣ መንፈስ አለመሆኑን ለማሳየት)
ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ፦
ዲያቆኑ በቅዳሴ ላይ ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ ይላል ፤ ሕዝቅኤል በትንቢቱ እንዲህ አንዳለ፦ “በምሥራቅ የተዘጋ ጀጅ አየሁ; ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም፤ ሰውም አይገባባትም ፤ የእስራኤል ቅዱስ ሳይከፍት ገብቶ ሳይከፍት ወቶባታልና” ሕዝቅኤል 44:1
ምሥራቅ እመቤታችን ናት ፤ መናፍቃኑ ግን ይህማ ስለቤተመቅደስ የተነገረ ነው ይላሉ; ተዘግቶ የሚኖር ቤተመቅደስ አለ እንዴ? ሰውም የማይገባበት ቤተመቅደስ የለም፤ ይህማ ስለእመቤታችን የተተነበየ ነው። ከምሥራቅ ፀሐይ እንደሚወጣ ከምስራቋ እመቤታችን ፀሐይ ጌታ ተወልዷልና። አንድም ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም አለ; ድንግል በክልኤት ናትና; በሥጋም በነፍስም ድንግል ናትና ፤ ቅድመ ፀኒስ ወሊድ ድንግል ፤ ጊዜ ፀኒስ ወሊድ ድንግል ፤ ድህረ ፀኒስ ወሊድ ድንግል ናትና; ወትረ ጊዜ ድንግል ናትና ሲል ነው። አንድም “ሰውም አይገባባትም” አለ አንድያ ልጇን ብቻ ወልዳለችና። የእመቤታችን ክብርማ መቼ ተነገረና? የእመቤታችን ፍቅርማ መቼ ተነግሮ ይፈጸምና? ስለፍቅሯ ለመዘመር ለመቃኘት…ሞከሩ ግን መቼ የእናቴ ፍቅር በቀላሉ ይነገርና? መቼ እንዲህ በቀላሉ?
“ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት”
እግዚአብሔር ፅዮንን መርጧታልና፤ ዛቲ ይዕቲ ምዕራፍየ ለዓለም (ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት) መርጫታለሁና በእርሷም አድራለሁ። መዝ 131:13
ሐዋርያው ዮሐንስ “ቃልም ሥጋ ሆነ” እንዳለ ጌታችን ከእመቤታችን ሥጋን ነስቶ ተወለደልን። ከእመቤታችን የነሳው ያ ቅዱስ ሥጋ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ብሎ ዐረገ። ክርስቲያን ሆይ ከእመቤታችን የተነሳው ያ ቅዱስ ሥጋ ወደሰማይ ዐርጓል እንጂ በምድር ተቀብሮ በስብሶ የቀረ እንዳይመስልህ። ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት እንዲል።
ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ዮሐንስ እንዲህ አለ፦
በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ … “ቃልም ሥጋ ሆነ” [ዮሐ1:1]
በመጀመሪያ ቃል ነበረ፦ “በመጀመሪያ” የሚለው ቃል “በመጀመሪያ” እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ ከሚለው ይለያል፤ [ዘፍ1:1] ሰማይና ምድር ለመፈጠር የተወሰነ ጊዜ ነበራቸው፤ በመጀመሪያ ቃል ነበረ የሚለው ግን በሰውኛ አገላለፅ እንዲገባን ነው እንጂ የተወሰነ ጊዜን አያመለክትም። ቁጥር እንኳን መጀመሪያና መጨረሻ የለውም፤ ቃል [ወልድ ዋህድ ኢየሱስ ክርስቶስም] የመጀመሪያው አልፋ የመጨረሻው ዖሜጋ ነው። ራዕ 22
በመጀመሪያ ቃል ነበረ አዎ ያም ቃል እግዚአብሔር ነበረ! ሥጋንም ለበሰ፤ ከማን? ከማን ሥጋን ነሳ? ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ በኤፍራታ በቤተልሔም ተወለደ!! ልበአምላክ ዳዊት ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ መዝ. [131:6] እነሆ በኤፍራታ ሰማነው እንዳለ ከሀገር ለይቶ በቤተልሔም ከቦታ ለይቶ በከብቶች ግርግም ከሴቶች ለይቶ ከእመቤታችን ተወለደ። ህጻን ተወልዶልናል ወንድ ልጅም ተሰቶናል አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙ ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም አባት የሠላም አለቃ ተብሎ ይጠራል። ኢሳይያስ 9:6
እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሰን!